ዋናኛ ገጽ (ወደ መነሻ ገጽ ይመለሱ > የአካዳሚክ ትምህርቶች > ኮሌጆች እና ትምህርት ቤቶች

የአፍሪካ ጥናቶች ትምህርት ቤት


非洲学院(1).jpg

የእስያ እና የአፍሪካ ቋንቋዎች ዲፓርትመንት በBFSU የተመሰረተው እ.ኤ.አ. በሴፕቴምበር 1961 ሲሆን ዋና ዓላማውም ከእስያ እና ከአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የወዳጅነት ግንኙነቶችን ለማጠናከር ነው። ስዋሂሊ እና ሃውሳ ቋንቋዎች በመጀመሪያ ከተቋቋሙት ዋነኛ ቋንቋዎች መካከል መካከል ናቸው።

በሴፕቴምበር 2019 ትኩረቱን በአፍሪካ ቋንቋዎች እና ጥናቶች ላይ ያደረገው የአፍሪካ ጥናት ትምህርት ቤት ራሱን ችሎ ተቋቋመ። በአሁኑ ጊዜ ትምህርት ቤቱ ስዋሂሊ፣ ሃውሳ፣ ኢሲዙሉ፣ አማርኛ እና ማላጋሲ ቋንቋዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ ይሰጣል። በተጨማሪም እንደ ሶማሊኛ፣ ሾና፣ ኪንያራዋንዳ፣ ኪሩንዲ፣ አፍሪካንስ፣ ታማዚት፣ ዮሩባ፣ ሴሶቶ፣ ሴትስዋና፣ ኮሞሪያን፣ ንዴቤሌ፣ ትግርኛ፣ ቺቼዋ፣ ሳንጎ እና ኢሲክስሆሳ ያሉ በርካታ የአፍሪካ ቋንቋዎችን በተመራጭ ኮርስ ደረጃ ይሰጣል።

በተጨማሪም ትምህርት ቤቱ በአፍሪካ ሥነ ልሳን፣ ሥነ ጽሁፍ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ አንትሮፖሎጂ፣ ፖለቲካ፣ ህግ እና ክልላዊ ድርጅቶች ላይ የሚያተኩር የአፍሪካ ጥናት ማዕከልም አለው። ትምህርት ቤቱ የድህረ ምረቃ፣ የዶክትሬት ዲግሪ እና የውጭ ሀገር ተማሪዎችን በየአመቱ በአፍሪካ ሥነ ልሳንና ሥነ ጽሁፍ እና አፍሪካ ጥናቶች ያተኮሩ ሁለት አካዳሚክ መርሃ ግብሮችንም ያካሂዳል።

ትምህርት ቤቱ በአፍሪካ ቋንቋዎች፣ ሥነ ጽሁፍ፣ ማህበረሰቦች እና ባህሎች ዘርፍ መምህራኑ የደረሱትን የቅርብ ጊዜ አካዳሚክ ስኬቶችን የሚያሳይ የአፍሪካ ቋንቋ እና ባህል ጥናቶች ጆርናል (Journal of African Language and Culture Studies) የተሰኘ በሁለት ቋንቋዎች በቻይንኛ እና እንግሊዝኛ የሚታተም ጆርናል አለው። በተጨማሪም ትምህርት ቤቱ በየዓመቱ በአፍሪካ ቋንቋዎች እና ባህሎች ጥናት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየም (International Symposium on African Languages and Cultures Studies) በማዘጋጀት በአለም ዙሪያ ያሉ ምሁራንን በመጋበዝ የአካዳሚክ ውይይት እና የልምድ ልውውጥ መድረክን ያስተናግዳል።

በተጨማሪም ትምህርት ቤቱ በአፍሪካ ከሚገኙ ከ20 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በዓለም ታዋቂ ከሆኑ የአፍሪካ ጥናቶች ተቋማት ጋር በአጋርነት ይሠራል፡፡ እነዚህም የምስራቃዊ እና አፍሪካ ጥናት ትምህርት ቤት፣ የለንደን ዩኒቨርሲቲ ፣ የእንግሊዙ የምስራቃዊ ቋንቋዎችና ሥልጣኔዎች ብሔራዊ ተቋም (SOAS) እና ከፈረንሳዩ (INALCO) ጋር አካዳሚክ አጋርነትን መሥርቷል።

ትምህርት ቤቱ 60 ዓመታት በላይ ባለው ታሪኩ የመማሪያ መጽሃፎችን እና መዝገበ ቃላትን የሥነ ጽሁፍን ትርጉሞችን እና የአካባቢ ጥናቶችን አዘጋጅቶ በማሳተም ረገድ ጉልህ ክንዋኔዎችን አስመዝግቧል በአሁኑ ጊዜ ትምህርት ቤቱ 16 ቻይናውያን መምህራን ያሉት ሲሆን ከነዚህ መካካል ሁለቱ ፕሮፌሰሮች፣ ሶስቱ ተባባሪ ፕሮፌሰሮች፣ ስምንቱ ደግሞ ፒኤችዲ ዲግሪ ያላቸው ናቸው። ከቻይናውያን የአካዳሚክ ባለሙያዎቹ በተጨማሪ ስምንት የውጭ ሀገራት መምህራን አሉ

አማርኛ የአፍሮ-እስያ ቋንቋ ቤተሰብ የሴማዊ ቋንቋ ሲሆን የኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ቋንቋ ነው። በኢትዮጵያ ከ 100 ሚሊዮን በላይ ከሆነው ህዝብ ከ80% በላይ የሚሆነው  አማርኛን እንደ አፍ መፍቻ ወይም ሁለተኛ ቋንቋ ይጠቀማል።

በዩኒቨርሲቲያችን የአማርኛ ቋንቋ ፕሮግራም ለመክፈት እ.ኤ.አ. በ2012 የተፈቀደ ሲሆን እ.ኤ.አ. ከሴፕቴምበር 2013 ጀምሮ አማርኛ በመራጭ ኮርስ ደረጃ ሲሰጥ ቆይቶ በሴፕቴምበር 2020 ፕሮግራሙን በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ በማሳደግ ተማሪዎቹን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ ይህም BFSUን  በአሁኑ ጊዜ በቻይና ውስጥ ብቸኛው አማርኛ ፕሮግራም የሚሰትበት ዩኒቨርሲቲ ያደርገዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሰፊ የማስተማር ልምድ እና ከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት ያላቸው አንድ ቻይናዊ አስተማሪ እና አንድ ኢትዮጵያዊ ረዳት ፕሮፌሰር መምህራን አሉት። ፕሮግራሙ የተማሪዎችን የአካዳሚክ አድማስ ለማስፋት በየጊዜው ከቻይና ወስጥ እና ከውጪ ባለሙያዎችን በመጋበዝ ስለ ቋንቋውና ስለ ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ለተማሪዎች ንግግሮችን እና ኮርሶችን እንዲሰጡ ይጋብዛል።  የአማርኛ ቋንቋ ፕሮግራም እ.ኤ.አ. በ2022 በቤጂንግ አንደኛ ደረጃ ያገኘ የቅድመ ምረቃ ትምህርት በመሆን ዕውቅና አግኝቷል፡፡

የአማርኛ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት ፕሮግራም ለአራት ዓመታት የሚሰጥ  ነው። በአንደኛ እና ሁለተኛ አመት ፊደላትን የመለየት፣ የሰዋሰው፣ የጥልቅ ንባብ፣ የንግግር፣ የማዳመጥ እና የመናገር ኮርሶችን በማቅረብ ተማሪዎቹ የቋንቋውን መሰረታዊ ክህሎት እንዲያዳብሩ የሚደርግ ነው። በሶስተኛ እና አራተኛ ዓመት የላቀ ደረጃ ያላቸው ኮርሶችን እንደ የዜና ንባብ፣ የትርጉም፣ የቃል ትርጉም፣ የሥነ ጽሑፍ፣  እና ባህል ያሉ የላቁ ኮርሶች ይሰጣሉ። በፕሮግራሙ የተማሪዎችን የአካዳሚክ አድማስ ለማስፋትም ብዙ የተመረጡ ኮርሶች ምርጫንም እንዲካተቱ ተደርጓል።

በተጨማሪም ተማሪዎቹ 3ኛ ዓመት ሲደርሱ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ትምህርታቸውን ከአንድ እስከ ሁለት ሴሚስተር የመማር እድል አላቸው። ይህም ለተማሪዎቹ ስለኢትዮጵያ የበለጠ እንዲጣውቁና የቋንቋ ችሎታቸውን ለማዳበር ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲያችን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የግንኙነት እና የትብብር ስምምነት አለው። ተማሪዎች በሚመዘገቡበት ጊዜ አማርኛን በዋና ኮርስነት እየወሰዱ እንደ እንግሊዘኛ፣ ዲፕሎማሲ፣ አለም አቀፍ ኢኮኖሚክስ እና ንግድ፣ ቢዝነስ አስተዳደር እና አካውንቲንግ የመሳሰሉትን የዲግሪ መርሃ ግብሮችን በንዑስ ፕሮግራም ደረጃ በመምረጥ ሌላ ሰርቲፊኬት ማግኘት ይችላሉ። በተጨማሪም ተማሪዎች ብሔራዊ የእንግሊዝኛ ፈተና ባንድ 4 እና ባንድ 8 በመውሰድ ሰርተፊኬት የማግኘት ዕድል አላቸው።

የአማርኛ ቋንቋ ኘሮግራም ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ጠንካራ እድገት አሳይቷል። በቻይናና በትምህር ክፍሉ ያለውን የመማሪያ መፅሐፍት ክፍተት የሚሞሉ “መሰረታዊ የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መፀሐፍ 1” “የቻይና ታሪክ እና ባህል ”፣ “የአማርኛ ንግግር” እና “800 የቻይንኛ ቃላት” የተሰኙ በርካታ የመማሪያ መጽሃፍት እና መዝገበ ቃላት ታትመዋል። በህትመት ሂደት ላይ ያሉም መፅሐፍት አሉ፡፡ ፕሮግራሙ ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ትኩረትና ድጋፍ የሚገኝም ነው። በፕሮግራሙን ለማበረታታት የቀድሞው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የፌደራል ፓርላማ አፈ ጉባኤ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እና በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደርን ጨምሮ በርካታ እንግዶች ዩኒቨርሲታችንን በመጎብኘት ተማሪዎቹን አበረታተዋል።

ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛዋ አገር ስትሆን የአፍሪካ ኅብረት ዋና  መቀመጫም ናት። እ.ኤ.አ በጥቅምት 2023 የቻይና እና የኢትዮጵያ መሪዎች የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ወደ በሁኔታዎች የማይቀያየር ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማደጉን አስታውቀዋል። ሁለቱ ወገኖች በተግባራዊ እና ወዳጃዊ ትብብር ፣በቅርብ ግንኙነት እና በተለያዩ መስኮች ትብብር በማድረግ ፍሬያማ ውጤቶችን አስመዝግበዋል። አማርኛ መናገር የሚችሉ ባለሙያዎችን የማግኘት  ከፍተኛ ፍላጎት ስላለ የአማርኛ ተማሪዎች ብዙ ሥራ ዕድል እንዳላቸው ይታመናል።