እኤአ የካቲት 4 ቀን 2026 የኡራጓይ ፕሬዝዳንት አማንዱ ኦርሲ ቤጂንግ ፎሪዬን ስተዲስ ዩኒቨርሲቲን (BFSU) ጎብኝተዋል። የBFSU ፓርቲ ኮሚቴ ፀሐፊ ፕሮፌስር ሊ ሃይ፤ የፓርቲ ኮሚቴ ምክትል ፀሐፊ እና የBFSU ፕሬዝዳንት ፕሮፌስር ጂያ ዌንጂያን፤ የፓርቲ ኮሚቴ ቋሚ ኮሚቴ አባል እና የBFSU ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌስር ዣኦ ጋንግ፤ በኡራጓይ የቻይና አምባሳደር ሁዋንግ ያዞንግ፤ በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ ዣንግ ዌንዌይ፤ እና የትምህርት ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ትብብር እና ግንኙነት መምሪያ ምክትል ዳይሬክተር ዣንግ ጂን በዝግጅቱ ላይ ተገኝተዋል።
ፕሬዝዳንት ኦርሲ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ሲሆን የቀድሞው የኡራጓይ ፕሬዝዳንት ሙጂካ በ2013 በተከሉት የቻይና-ኡራጓይ የወዳጅነት ዛፍ ጋ ተገኝተው ከፕሮፌስር ሊ ሃይ እና ፕሮፌስር ጂያ ዌንጂያን ጋር በመሆን ዛፉን አፈር በማሰታቀፍ ውሃ አጠጥተዋል፡፡ አዲሱን የወዳጅነት ዛፍን መግለጫ ሰሌዳ ከፍተዋል። ፕሮፌስር ሊ ሃይ ለፕሬዝዳንት ኦርሲ የወዳጅነት ዛፉን የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል።

ይህንን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ኦርሲ እና የልዑካን ቡድናቸው የወንኋ አዳራሽን ጎብኝተው የስፓኒሽ ቋንቋ ትምህርት የሚሰጡ ከ16 ዩኒቨርሲቲዎች እና ከቤጂንግ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመጡ መምህራን እና ተማሪዎች ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል። ሥነ ሥርዓቱ የተመራው በፕሮፌስር ጂያ ዌንጂያን ነበር።
በስብሰባው ላይ ፕሮፌስር ሊ ሃይ ቤጂንግ ፎሪዬን ስተዲስ ዩኒቨርሲቲን (BFSU) በመወከል ለፕሬዝዳንት ኦርሲ የእንኳን ደህና መጡ ንግግር አድርገዋል። BFSU ከኡራጓይ ጋር ያለውን የቅርብ ትብብር ሁልጊዜ እንደሚያጠናክር ገልፀው የሁለቱንም ሃገራት ቋንቋዎችና ባህሎችን የሚያውቁ በቻይና እና በኡራጓይ መካከል ወዳጅነትን የሚያጎለብቱ ወጣት አምባሳደሮችን ለማፍራት ከኡራጓይ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከአካዳሚክ ተቋማት ጋር ጠንካራ ግንኙነት እና ትብብር ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልፀዋል።
ፕሬዝዳንት ኦርሲ ባደረጉት ንግግር በአገሮች መካከል ጤናማ እና የተረጋጋ ግንኙነት እንዲኖር ዋነኛው ጉዳይ የጋራ መተማመን እንደሆነ እና የአካዳሚክ ግንኙነቶችም ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ገልፀዋል። በቻይና እና ኡራጋይ እንዲሁም በቻይና እና በላቲን አሜሪካ መካከል ያሉት የአካዳሚክ ግንኙነቶች ጥልቅ የትብብር ደረጃን የሚወክሉ ከመሆናቸውም በላይ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለማጠናከር መሰረት የሚጥሉ ናቸው። ሁለቱም ወገኖች እርስ በእርሳቸው ከተሞክሮዎቻቸው መማር፣ የእውቀትና ምሁራዊ ውስንነቶችን ማስወገድ እንዳለባቸውና በጋራ በመተባበር እና በመነጋገር ሰላምን እና ልማትን ማበረታታት እንደሚችሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ኦርሲ ከንግግራቸው በኋላ በዝግጅቱ ላይ ከተገኙት መምህራንና ተማሪዎች ጋር ተወያይተዋል። ፕሮፌስር ሊ ሃይ የBFSU መምህራንና ተማሪዎችን ወክለው ለፕሬዝዳንት ኦርሲ በBFSU የስፓኒሽና የፖርቱጋል ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሳሉትን የቻይናና የኡራጋይን ወዳጅነትን የሚያሳይ የዛፍ ሥዕል ለፕሬዝዳንት ኦርሲ አበርክተዋል።
ዝግጅቱ ከመጀመሩ በፊት ፕሬዝዳንት ኦርሲ የBFSU የስፓኒሽ ቋንቋ ትምህርት ፕሮግራም ስኬቶችን የሚያሳይ ኤግዚቢሽን ጎብኝተው አስተያየታቸውን በፅሁፍ አስፍረዋል። ከዚያም ከBFSU የስፓኒሽ ቋንቋ ፕሮግራም የተውጣጡ ተማሪዎች ሙዚቃ ያቀረቡ ሲሆን ተመልካቾች አድናቆታቸውን በጋለ ጭብጨባ ገልፀውላቸዋል።
የኡራጓይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሉቤቴኪን፣ በቻይና የኡራጓይ አምባሳደር ካብራል፣ የእንስሳት እርባታ፣ የግብርና እና የአሳ ሀብት ሚኒስትር ፍራቲ፣ የኢንዱስትሪ፣ የኢነርጂ እና የማዕድን ሚኒስትር ካርዶና እና ሌሎች የልዑካን ቡድኑ አባላት በዝግጅቱ ላይ ተሳትፈዋል።